ገበሬውና ሚስቱ (THE FARMER AND HIS WIFE


በተፈሪ ደፈረሱ (ዘደብረ ሊባኖስ) የተደረሰ፣ እትም ፲፱፻፵፱፣ የተረዳ (ኢለስትሬትድ) ግጥመ-ልብወለድ ነው።

 • ትልም


ሁለት ጥንድ ገበሬዎች በድህነት፤ ግን በአክብሮት፤ ሲኖሩ የሚስት ጥብቅ መካሪነት፣ አስተዋይነት፣ እና ብሩህነገን ናፋቂነት የተሻለውን ጊዜ ፈጥሮ አስደሳች እና ስኩ ቤተሰባዊ ህይወቶች ሲመጡ ያሳያል። የድሀድሀ ገበሬ በረሀብ የሚስቱን ትእግስት ይፈትናል። ሚስት ነገርግን ታጋሸነትን በመስበክ ባሏን ጥቅመ ቁጠባን አጣፍጣ ታስተምራለች።

እንደተለመደው በእየለቱ ያለውን ምግብ በመመገብ ለነገ ባዶ ከመሆን ይልቅ፣ ከተለመደው ውጭ ምግቡን እያሻገሩ ተርበው በመቆጠብ እንዲኖሩ ታደርጋለች። መራራ ህይወታቸውን ለመቀየር ሚስት ባሏን በማነሳሳት፣ በቀለብነት ያጎደለችውን ዘር በልመና ከቤቶቿ (የቀድሞ ቤተሰብ) ተበድራ በማግኘት ሐምሌን እንዲያርስ ታደርጋለች። እስከ ጥቅምት ድረስ በጥን ችግር፤ ግን በስረ ማሳው እንደጠነከሩ፤ ጥቅምት ውስጥ በትኩስ እሸቶች ይንበሸበሻሉ። ከብቶቻቸውም አርሰዋልና-ሰብል-እስኪደርስልን-ይሸጡ-ከሚለው ቅድመ-መኸር የአስገዳጅ-መፍትሔነት በሚስት ቁጡ ውሳኔ ተረፉ፨

በህዳር፤ ለድግሱ የእህል ግብአቶችን ተበድረው፣ ደቦ ይጠራሉ። የስረ ማሳቸው ስኬት ዜና ተሰምቶ የበቀለው ታጭዶ ባል በሚትስ ፈቃድ የስራእድል የለመነውን አጋዥ እንዲሆነው ይቀጥራል፤ ለሷም ደንገጡር አርጉኝ ያለችን ይቀጥራሉ። ህይወታቸው በኑሯቸው ተሻሽሎ፣ እዳዎቻቸው ተመልሰው፣ በማህበረሰቡ ተከብረው፣ የካቲት ላይ በደስታ ግብር ከፍለው፣ ወደሚስት ቤቶች ብዙ ስጦታ አስይዘው ከቀጠሯቸው ጋር ለፋሲካ አክፋይ፣ በዚህኛው ጊዜ ብልፅግ አስችሏቸው፣ ይሄዳሉ። ደስተኛ ጊዜ አሳልፈው “ሰው መሆናቸውን” ካሳዩ ወዲያ፣ የተክሊል ሀሳብ ይነሳና ይስማሙበታል። በተክሊል ጋብቻቸውን ዳግመኛ አጽንተው ይሰነብቱና፤ ገንዘባዊ ድጋፍንም ጨምረው፣ ተመርቀው እና ለወደፊቱ ሀይማኖተኛ ቤቶቿን ለመርዳት ብቁነታቸውን አሳይተውና ለዚሁም እንዲጠየቁ አሳውቀው ከተሳካ ሽርሽራቸው ወደ መንደራቸው ተመለሱ። ሁሉም የተውት ንብረት እንደነበር ጠበቃቸው። ዞሮ ሲመጣ፤ ተለውጠው ግንቦትን ተቀበሉት፤ ይህ ሁሉ ሰው የመሆን ሚስጥር ጠንክሮ መስራት መሆኑን ይወያያሉ፨

 • መተንትነ ጭብጥ


ትህትና እና አክብሮት ያለበት ጋብቻ በጠንክሮ መስራት የቤተሰብን ስነምጣኔያዊ ችግሮች አስወግዶ ሀብትና የበለጠ ፍቅርን ይሰጣል። ይህ የትልሙ ጥንክር ነው። በዚህ ስር ጭብጡ ይሽከረከራል። ለውጥን፣ በተለይም የሚቋምጡትን ኑሮ-ውጤት፣ በራስ ጥረት ሄዶ-ማምጣትን ይሰብካል።

ይህም ዉጤት የሚያካትተው፤ አንደኛ፣ ከተግባር ቀድሞ በውይይት ተመንጭቶ የነጠረ እና የጠነከረ ንድፈሀሳባዊ (ስሌት) ግቤት፤ ሁለተኛ፣ የታቀዱትን አስፈላጊ ቁሳቁሶቹን ማሟላት፤ ሶስተኛ፣ በትግበራ የጥንክር ተጋድሎሽ ናቸው። በመጨረሻ አራተኛ፤ ከቀደሙት ግን ሳያንስ፤ ቀናዊነት እና በሚተርፈው ሁሉ አምላክን መጠየቅና ማመንን ነው። የሚቀጥለው ተፈላጊውን ውጤት ይመጣልና እሱን ማጣጣም ነው። የመፅሐፉ ፍሬነገር ትኩረት በነዚህ ሂደቶች ላይ፤ ከተግባር የሚቀድሙ የጥልቅ ውይይቶች፣ በሂደቶች ሁሉ መከባበር እና በጋራ መስራት የሚፈጥሩትን አንፀባራቂ መስተጋብር ማየት ነው፨

የመፅሀፉ ዋነኛ ሀሳብ፣ አሁንም ቢሆን አግባብነት አለው። ኢትዮጵያ ካሏት ሁነኛ እና የሁልጊዜም ችግሮች መሀከል አንዱ የዜጎች ራስን መመገብ አለመቻል ነው። አብዛኛው ክፍለአለም በስልጣኔ መርቀቅ ላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያዊያን ፫ ሺህ ዘመናት ተሻግሮ አሁንም ድሀድሀ መሆን በዜጎቿ ጠንክሮ አለመስራት እንደሆነ አስቀድሞ በመቀበል፣ መውጫ መንገዱን ለመቅረፅ መሰረቱ ብልህ የሆነ ግላዊ ጥረቶች እንደሆኑ የመፅሀፉ የሀሳብ ሙከራዎች ያስረዳሉ፨

• ከተጋሩ እይቶች


 ትልም፣ ታሪክና ገፀባሕሪያት ውስጥ የተንሸራሸሩ መልእክቶች፤

፩. ጣፋጭ ትዳራዊ እግዝ እና አክብሮት፤

፪. ሁሌም ተማምኖ-አምላክ (ሁነኛ የኢትዮጵያዊያን መገለጫቸው)፤

፫. ሚስት ለባሏ ዘውድ፤ ማለትም ከሌሎች ነገሮች መሀል፣ ምንጨ ለውጥ እና ለነገረመልካም ምሪት መሆኗን፤

፭. ውስጠ ቤት ስነምጣኔ (ሖም ኤኮኖሚክስ)፤

፮. የጥረት ስኬት፤

፯. በሀላፊነት ራስን ማበልፀግ እንጅ ሌሎችን መመልከት እንዲያሳፍር፤

፲. የትብብር ስኬት፤

፲፩.የሌሎችን ፍላጎት ለራስ መጠቀሚያ ስለማድረግ፤

 • አንዳነድ ምርጥ ጥቅሶች


 # ገበሬና ወላድ ባምላክ አያማርርም፣
ዛሬ ይስጠው ነገ የእድሉን አያውቅም። (ገ. ፲፱)

# ያቺ የሐምሌ ወር ችግሯ እንዲያ ሲመር፣
እሷስ አውቃው ኖሯል መሆኗን የጥቅምት ማር። (ገ. ፳፪)

 # አጫጁን ማሳጨድ ቀላል ነው መንገዱ፣
ባፍ እየደለሉ መስጠት ነው ለሆዱ። (ገ. ፴፫)

 # የሰራውን ስራ አልቆለት እስኪያይ፣
ቸልተኛ መሆን በፍፁም አያሻም፣
መሥራት ነው መድከም ነው ለማግኘት ሁሉንም። (ገ. ፴፯)

 # ካልሰራን ካልደከምን አርቀን ካላሰብን፣
ባምሳሉ ተፈጥረን እርዱኝ እንድረዳችሁ ማለቱን እያወቅን። እንድንሠራበትም ዓይን እጅ እግር ሰጥቶን ቀድሶ ባርኮናል፣
እንግዲህ ለማግኘት ማሰብና መስራት እወቀው ያሻናል። (ገ. ፴፮)

 # የሰው እጅ ማየት ሁለተኛው ሞት ነው። (ገ. ፴፮)

 # ሰው ሆኖ ተፈጥሮ የማያይ የኋላውን፣
ዛሬም ሰው አይደለ ለወደፊቱም አይሆን። (ገ. ፴፯)

 # የሰው ልጅ ከዶሮ በምን ምክያት ያንሳል፣
እሱ እንኳ ባቅሙ ቆፍሮ ይበላል። (ገ. ፴፯)

 # እኔ አንተን ስቀጥር እኔን የቀጠረችኝ፣
ተዋበች የሚሏት አንድ ሚስት አለችኝ። (ገ. ፴፱)

 # በቅን ከተሰራ በንፁህ ልቦና፤
እሱስ ቅርብ ኖሯል የማግኘት ጎዳና፣
ወደኋላ ሳየው የነበርንበትን፣
የዛሬውን ስናይ አሁን ያለንበትን፣
ሰው እንዴት ይጠላል ሥራና ሕብረትን። (ገ. ፵፩)

 # ምንም ሴቶች ብንሆን ግዴለም አትናቁን፤
ያለኛ እንደማይሆን እወቁት እቅጩን፤
በማንኛውም በኩል ረዳቶቻችሁ ነን። (ገ. ፵፰)

 # ሰውም ከሠራና አምላክም ከሰጠው፤
ብዙ ጊዜ አይፈጅም ዕለት በዕለት ነው። (ገ. ፶፯)

 # በብዙ ሰዉ ፊትም ሰው ለመሆን የቻልነው፤
በመተባበርና ጠንክሮ በማረስ ነው። (ገ. ፶፰)

                    --------
ቢንያም ኃይለመስቀል፤ ፪፻፻፲፪ እኢአ

Comments

Popular posts from this blog

SOME POPULAR ETHIOPIAN SAYINGS AND PROVERBS WITH THEIR TRANSLATION AND EXPLANATION IN ENGLISH. 2

SOME POPULAR ETHIOPIAN SAYINGS AND PROVERBS WITH THEIR TRANSLATION AND EXPLANATION IN ENGLISH.1

SOME POPULAR ETHIOPIAN SAYINGS AND PROVERBS WITH THEIR TRANSLATION AND EXPLANATION IN ENGLISH. 8